ቅዳሜ 6 ኤፕሪል 2013

የቀበጡ እለት ሞት አይገኝም ከቴዲ አፍሮ ወደ ቅዱስ ገብሬል (መልካምሰው አባተ)

ከአመታት በፊት አንድ ቀን በጣም አንቀለቀለኝ፡፡ ጠገብኩ፡፡ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮን በመተቼት ጋዜጣ ላይ ፃፍኩ፡፡
ከአድናቂ ጋር የሚያጣላ ነገር እንዳልጻፈ ሰው በነጻነት በሰፈሬ እዞር ነበር፡፡ ደፋር እኮ ነኝ፡፡ ቴዲ አፍሮን
የሚያክል ‘ጣኦት’ ተችቶ በነፃነት መዞር? የእንጦጦን ነፋስ ለመቀበል ከአዲሱ ገበያ ተነስቼ ወደ ላይ
እንጎራደዳለሁ፤ በኩራት፡፡ የቴዲ አፍሮን ምስል የለበሱ አምስት ወጠምሻ ወጣቶች ተጠጉኝ፡፡ መጀመሪያ አልፈራሁም፡፡
ዙሪያዬን በአምስት ጎረምሳ ስታጠር ግን ተንቦቀቦኩ፡፡ አንገቴ ስር ጫማ ጥፊ ገብቶልኝ ከመውደቄ በፊት አንድ ዙር
አማተርኩ፡፡ ዙሪያዬን ከበውኛል፡፡ አጠር ቀጠን ያለውን አድናቂ ገፍትሬው ወደ ሰሜን ሸመጠጥኩ፡፡ ተከተሉኝ፡፡
ስንሮጥ እንጦጦ ደረስን፡፡ የጎጃምን መስመር ይዤ እፈተለክ ቀጠልኩ፡፡ እንዲህ እንደምሮጥ አላውቅም ነበር፡፡ ‹‹ሩጫ
ለነ ቀነኒሳ ብቻ የተሰጠ ፀጋ ይመስለኝ ነበር፡፡›› ስል እያሰብኩ እሮጣለሁ፡፡ አባራሪዎቼም ይከተሉኛል፡፡ የዋዛ
አድናቂዎች አልነበሩም፡፡
‹‹ምን ያህል ቢያደንቁት ነው? ወይኔ ሰውዬው! ትምህርት ትቼ ብዘፍን ኖሮ ልቡ እስክትፈርጥ ድረስ የሚሮጥልኝ
አድናቂ ይኖረኝ ነበር፡፡ አባቴ ግን ሸወደኝ፡፡ ተማር ተማር እያለ የብርም የአድናቂም ድሃ አደረገኝ፡፡ ወደትምህርት
ቤት ሂድ ከሚለኝ እንደ አቶ አፍሮ ወደ አገር ቤት እያልክ ዝፈን ቢለኝ ምን ነበረበት?›› ስል እየተቆጨኹ
እሮጣለሁ፡፡ ሩጫ ከቁጭት ጋር አይሄድም፤ ያደክማል፡፡  ….ብቻ እንደ ቀነኒሳ ኋላዬን ገልመጥ እያልኩ እያየሁ እሮጣለሁ፡፡
ሱሉልታን አለፍኩ፡፡ አቤት ዳገቱ፡፡ ሮጥኩ፡፡ ሮጥኩ፡፡ ሮጥኩ፡፡ ሰላሌ ሜዳ ላይ ስደርስ ሩጫዬን ጨረስኩ፡፡ ሰው
እንዴት ዳገቱን አልፎ ሜዳው ላይ ሲደርስ ሩጫውን ይገታል? ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ ተስፋ በቆረጠ ሁናቴ ወደ ኋላ ዞር ብዬ
ሳማትር አባራሪዎቼም ሩጫቸውን ጨርሰው ኖሯል፡፡ ተመስጌን አልኩ፡፡ አንደኛው ብቻ ተስፋ በመቁረጥና ተስፋ በማድረግ
መካከል ሆኖ ልሩጥ ልተወው እያለ በጥቂት ሜትሮች ከእኔ ኋላ ቆሟል፡፡ ትንሽ ቢሮጥ እኔ ነዳጅ ስላልነበረኝ ሊይዘኝ
ይችል ነበር፡፡ እግዚሃር ይስጠው መሮጡን ትቶ መሳደብ ጀመረ፡፡ ‹‹ቆይ ጠብቅ አንተ ውሻ! አንተ ነህ ቴዲዬን
የምትሳደበው? ሽንታም! ፈሳም! በቀቀን!…..፡፡ ስማ ደግሞ በዛው ንካው ወዳገርህ ወደ በጌ ምድር፡፡ በግ የበግ
ልጅ እንዲሁም የፍየል፡፡ ገበሬ ነህና ወደ ግብርና ትመለሳለህ እንጅ አዲሳባን ዳግም አትረግጣትም፡፡……›› አለና
ግራ ኋላ ዞሮ ተመለሰ፡፡ እኔም መንገድ ዳር ቆሜ ከበጌ ምድር አቅጣጫ የሚመጣ መኪና እጠብቅ ጀመር፡፡ አንድ እንጨት
የጫነ አይሱዙ ከጎጃም ሲመጣ አየሁ፡፡ ሲደርስ እጄን አውለበለብኩለት፡፡ ሾፌሩ አቆመልኝ፡፡ ‹‹ጋቢና ሙሉ ስለሆነ
ከላይ ውጣ!› አለኝ ሾፌር፡፡ ወጣሁ፡፡ አይሱዚው ትንሽ እንደሮጠ አሯሩጠውኝ ከተመለሱት አድናቂዎች ጋር ደረሰ፡፡
አባራሪዎቼ የመንገድ ዳር ይዘው ወዳገራቸው ወክ ያደርጋሉ፡፡ አይሱዚው እና እኔ አጠገባቸው ስንደርስ እጄን
አውለበለብኩላቸው፡፡ ባለማመን እና በንዴት ፊታቸው ጉበት ሲመስል ታዬኝ፡፡ ወደ አዲሳባ ቀድሜያቸው ስመለስ እኔን
የተሰማኝ ሃሴት እነሱን የተሰማቸው ንዴት ቢጋጭ 6 ሺ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኤነርጂ ይፈጥር ነበር፡፡ አጋነንኩ
እንዴ? እሺ 60 ሺ ይሁን፡፡
አንደኛው አድናቂ አይሱዚው ላይ መሆኔንም እያዬ በሩጫም ሊከተለኝ አማረው፡፡ ሮጠ፡፡ ቆይቶ ሲያስበው መኪና ላይ ነው
ያለሁት፡፡ ሩጫውን አቆመ፡፡ ቢሮጥ ፈልጌ ነበር፡፡ ምናልባትም ፈጣን ሯጭ ሆኖ አይሱዚውን ሊደርስበት ይችል ይሆን
ነበር፡፡ ይህም ማለት አገሬ የ800 ሜትር ሯጭ አገኘች ማለት ይሆን ነበር፡፡ ከአድናቂነት ወደ ተደናቂነትም
ይሸጋገር ነበር፡፡ ለጀግና በመዝፈን ጀግንነቱን ያስመሰከረው እና አጥር ያልተበጀለት የዝና ኢምፓዬር የመሰረተው ቴዲ
አፍሮም ይዘፍንለት ነበር፡፡
*
*****                           *
በሌላ አንድ ቀን ማለትም በቀደም አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ቁጭ ብዬ ሻይ እየጠጣሁ የቀጠረኝን ጓደኛዬን
እጠብቃለሁ፡፡ አንድ የራሱን ምስል በቲሸርት አሳትሞ የለበሰ ወጣት ወደ እኔ መጣ፡፡ ሰላም አለኝ፡፡ ሰላም
አልሁት፡፡ ተሰላለምን፡፡
‹‹አስታወስከኝ?›› አለ፡፡
‹‹ãረ በፍፁም!››
‹‹አንዴ ቴዲ አፍሮን በጋዜጣ ተችተኸው ከጓደኞቼ ጋር ልንደበድብህ ስናባርርህ ነበር፡፡ ትዝ አለህ?››
‹‹አሃ፤ ትዝ አለኝ፡፡ እና አሁንም እንሯሯጥ እያልከኝ ነው?›› አልኩት፡፡
ሳቀ፡፡
‹‹ቁጭ በል፤ ቁጭ ብለህ አውራኝ!››
ተቀመጠ፡፡
‹‹በውነቱ ያኔ ተሳስተናል፡፡ በእኔና በጓደኞቼ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ መለስ ዜናዊ የሰጠህን የመፃፍ መብት እኛ
ልንነጥቅህ መነሳታችን መለስን ቅዱስ እኛን እርኩስ ያደርጋል፡፡ ኦባማ እንዳለው የመፃፍ መብትን በመንፈግ ከመለስ
ዜናዊ አንሶ መገኘት ማለት ደግሞ ሞት ማለት ነው!›› አለ፡፡
አባባሉ አንጀቴን በላው፡፡ ደግሞም አደነኩት፡፡ በልቤ ውስጥ የነበረችኝን ይቅርታ አንድም ሳላስቀር አውጥቼ
ሰጠሁት፡፡ ኪሴ ውስጥ ገንዘብ ቢኖረኝ ኖሮም ልስጥህ ባልኩት ነበር፡፡ በውነቱ አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ከዘፋኝ
ተከታይነት ወጥቶ በራሱ ፍልስፍና እየኖረ የሶቅራጥስን የሚያክል ጥቅስ ሲናገር መስማት የደስታ ለቅሶ ያስለቅሳል፡፡
ሆኖም በወቅቱ በአዲሱ የሊዝ አዋጅ ምክንያት አጎቴ ቤቱን በተከራዩ ስለተቀማ ለቅሶ ላይ ስለነበርኩ እና እንባዬንም
ስለጨረስኩት ሳላለቅስ ቀረሁ፡፡
‹‹በጣም አመሰግናለሁ!›› አልሁት፡፡
‹‹ማመስገን ያለብኝማ እኔ ነኝ፡፡ ይገርምሃል ያኔ እስከሰላሌ ሜዳ አንተን ከማባረራችን በፊት እኔና ጓደኛቼ ወንድ
ልጅ አባረን አናውቅም ነበር፡፡ ሴት ነበር የምናባርረው፡፡ በዚህ የተነሳ ፒያሳን እንጂ ሰላሌ ሜዳን አናውቀውም
ነበር፡፡ አንተን ከማባረራችን በፊት እኔም ጓደኞቼም ከአዲስ አበባ ወጥተን አናውቅም፡፡ በተለይ እኔ ከአዲስ አበባ
ውጭ የማውቀው ሩቅ አገር ቃሊቲ ነው፡፡ ዛሬ ግን ዕድሜ ላንተ ታሪከ ተቀዬረ፡፡ ጧት እንጦጦ ብትመጣ እኔን
አታጣኝም፡፡ እንጦጦ ብታጣኝ እንኳ ሰላሌ ሜዳ ታገኘኛለህ!›› ሲል አብራራ፡፡
‹‹እንዴት?›› ስል ጠየኩ፡፡
‹‹ያኔ አንተን ሳባርር ነው እግዜር የሰጠኝ ተሰጥኦዬ ሩጫ መሆኑን ያወኩት!››
‹‹ግንኮ ሮጥክ እንጂ አልያዝከኝም?!››
‹‹ባልይዝህም ሯጭ መሆኔ ገባኝ፡፡ እናም እሮጥ ጀመር፡፡ ዛሬ በክለብ ታቅፌ ክለቤና አገሬ የሚመኩብኝ ሯጭ
ሆኛለሁ!›› አለ፡፡
በውነቱ እጅግ በጣም ደስ አለኝ፡፡ አንድ ያገሬ ልጅ እኔን ተመስሎ ተሰጥኦውን ሲያገኝ እንዴት አልደሰት፤ ለዛውም
ሩጫን የመሰለ ተሰጥኦ፡፡ ከራስ አልፎ አገር የሚያስጠራ ታላቅ ሙያ፡፡ እግዜር አንድን ሰው ሊለውጥ ሲፈልግ መልዓኩ
ገብሬልን ነው የሚልከው፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ግን እኔንም ይልከኛል መሰል፡፡
‹‹በነገርህ ላይ ያኔ ስታሯሩጡኝ አንድ የረሳችሁት ነገር ነበር!›› አልሁት፡፡
‹‹ምን?››
‹‹እኔም እንደናንተ የቴዴ አፍሮ ዘፈኖች አድናቂ መሆኔን፡፡ ልዩነቱ እናንተ ሰውዬውን እኔ ሙዚቃውን መውደዳችን
ነው፡፡ እግዚሃር በየለቱ በሚጎበኛት አገር የሰው ጣኦት መፍጠር ጥሩ አይደለም፡፡ በጋኔን ያስመታል!›› አልኩት፡፡
‹‹እግዜር ኢትዮጵያን በየለቱ ይጎበኛታል ብለህ ታምናለህ እንዴ?››
‹‹ሌላ ምን ምርጫ ይኖረዋል፡፡ ወደ ሰሜን ቢያይ አመፀኛ፤ ወደ ደቡብ ቢቃኝ የባህር ወንበዴ፣ ወደ ምዕራብ ቢያማትር
ግብረሰዶማዊ፤ ምስራቅ ቢያቀና አላውቅህም የሚለው ትውልድ ይገጥመዋል፡፡ አንገቱን ነቅንቆ ወደኛው ይመለሳል፡፡
አያያዙን ስተነው እንጂ የዘመኑ አብርሃሞች እኛ ነበርን!›› አልኩት፡፡ የሰማኝ አልመሰለኝም፡፡
‹‹ይገርምሃል፡፡ ዘፈን ከመውደዴ የተነሳ ዘፋኝ ማምለክ ጀምሬ ነበር፡፡ ይሄ ራስን መናቅ ከእግዜር መራቅ መሆኑ
ሲሰማኝ ራሴን ጠላሁ፡፡ ተፀፀትኩ፡፡ የሩጫ ክህሎቴ ደግሞ አፅናናኝ!›› አለ፡፡
‹‹ጥሩ አድርገሃል፡፡ ያኔ ግን ብትይዙኝ ኖሮ ምን ታደርጉኝ ነበር?›› ስል ጠዬኩ፡፡
‹‹እንደ መጥምቁ ዮሃንስ አንገትህን እንቆርጠው ነበር፡፡ የሄሮድስ እርኩስ መንፈስ በዘፈን ታዝሎ አናታችን ላይ
ሰፍሮ ነበር!›› ሲል መለሰ፡፡
ዘገነነኝ፡፡ ‘’ገረፍ ገረፍ አድርገን እንለቅሃለን!” የሚል ነበር የመሰለኝ፡፡ ወይ ጉድ፤ ከሞቴ አሟሟቴ፡፡ አገሬ
በሴቶች ጉዳይ ብቻ ትጨነቃለች፡፡ እንዲህ አይነት የወንዶች ጉዳይ መኖሩን ሳታውቅ፡፡ አይ የዛሬ ልጅ፤ አባቶቹ
ለእናት አገራቸው ፈረንጂ ሲገሉ ቢያይ እሱ ለዘፈን እኔን ወንድሙን ሊገድል ተነሳ፡፡ በዚህ የተነሳ ‘’አለም ላይ
የመጀመሪያው ማህበራዊ ብርሃነ ህሊና (social enlightenment) የታዬው በኢትዮጵያ ሲሆን የመጨረሻው
ማህበራዊ ዝቅጠት (social depression) የተከሰተውም በዚችው በኢትዮጵያ ነው’’ ብለው የፃፉትን
ምዕራባውያን ፀሃፍት ላምናቸው ወሰንኩና ከአርበኝነቴ ጋር ስለማይሄድ ተውኩት፡፡ ግን በጣም ነበር የከፋኝ፡፡ እስኪ
አንባቢያን አስቡት፤ በዘፈን ሰበብ የሞት እጩ ሆኖ ከመቅረብ የባሰ ምን አስከፊ ነገር አለ?!
‹‹ብቻ ግን ገብሬልዬ ጠበቀን፡፡ ትዝ ይልህ ከሆነ ያኔ ያሯሯጥንህ በገብሬል ዕለት ነበር፡፡ ሰው ከመግደል
የዳንኩበት ሩጫ እንደምችል የተረዳሁበት ቀን ስለሆነ በየወሩ ገብሬልን እዘክራለሁ፡፡ በመጭው ገብሬል የትም
እንዳትሄድ እኔ ቤት ነህ፡፡ ዳቦ ትቆርሳለህ!›› አለ፡፡
‹‹በል በየወሩ በ19 እቤትህ አልቀርም፡፡ በውነቱ ከቴዲ አፍሮ ወደ ገብሬል ያደረከው ሽግግር ወይም ዕድገት የፎቅ
እንጂ የአስተሳሰብ ዕድገት ለማይታይባት አገራችን አስደናቂ ዕድገት ስለሆነ በታላቅ ምሳሌነቱ አገር ቢያውቀው ምን
ይመስልሃል?›› አልኩት፡፡
‹‹ጥሩ ነው፡፡ ፃፈው፡፡ ይሄን ለለውጥ የተዘጋ ህዝብ በደንብ ስደብልኝ ደ’ሞ፡፡ ምነው እንዳንተ መፃፍ በቻልኩ ልክ
ልኩን እነግረው ነበር!›› አለ፡፡
‹‹ãረ በገብሬል ይዤሃለሁ፤ ህዝብ እንደዚህ አይባልም፤ ህዝብ እኮ እግዜር ማለት ነው?!›› አልኩት ኮስተር እና
ኩምትር ብዬ፡፡
‹‹ãረ እባክህ! እሱን ብሎ እግዜር፡፡ ለነገሩ ቢሰድቡትስ ይሰማል ብለህ ነው፡፡  በፓርላማ መዶሻና እና በዘፋኝ
ማይክራፎን ደንቁሮ!››
‹‹አንተ ራስህን ከለወጥክ ይበቃል፡፡ ሌላውም እንዳንተ ሲለወጥ ባንድ ላይ አገር ይለወጣል፡፡ ሒሳቡ እንደዚህ
ነው፡፡ ከዚህ ወዲያ ራስህን እንጂ ሰው አትከተል!››
‹‹አዎ፡፡ በተለይ ዘፋኝ አልከተልም፡፡ ዘፋኝን ብትከተለው ጥሩ ቦታ ወሰደህ ቢባል  ስቱዲዮ ነው፡፡ እንደ ስቱዲዮ
የጠበበ የአለም ክፍል ደግሞ የለም፡፡ የኮንዶሚኒዬም ጠባቡ እንኳ ስቱዲዮ ይባላል፡፡……›› አለ፡፡
የመሳቅም የማውራትም ስሜት አንድ ላይ መጣብኝ፡፡ ማውራቱን አስቀደምኩ፡፡
‹‹በዚህ እንኳን አልስማማም፡፡ አንዳንዴ ከጠባቡ የስቱዲዮ አለም የሚወጡ ዘፈኖች ለአለም መፍትሄ ሲያመጡ ታይቷል፡፡
ጦርነትና ሰላም ያልፈታውን ዘፈን ፈቶት ያውቃል፡፡ ለምሳሌ የቴዲ አፍሮ ‘ኻብ ዳህላክ’ የተቆረጠ የኢትዮጵያን ብርሌ
አንገት መልሶ የሚቀጥል ይመስለኛል!›› አልኩት፡፡
‹‹………ብለን ተስፋ እናድርጋለን፡፡ ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ ያገሬ ዘፈን ግን ከአንሶላ ውስጥ ወግ አልወጣም፡፡ የአንሶላ
ውስጥ ወግ ከኦርጋዝም ዘዴ በስተቀር ምን ይነግርሃል!? ለሱ ለሱማ እኛም አናንስም….›› አለ፡፡  በጣም ሳኩ፡፡
‹‹ወደፊት ከአንሶላ ወጥተው እንደሚዘፍኑ ተስፋ እናደርጋለን!››
‹‹ብርዱን ይችሉታል ብለህ ነው?››
‹‹ቴዲ አፍሮ ከአልጋ ወርዶ ከቤተመንግስቱ ማማ ላይ ወጥቶ በመለስ መላጣ አንዣቦ ቀጥሎም ቃሊቲ ገብቶ ብርዱ
እንደሚቻል ያሳያቸው መሰለኝ!››
‹‹አይ፤ የቃሊቲን ብርድ እንኳ እንዳልቻለው አረጋግጠናል፡፡ ቃሊቲ የፖለቲካ አቋሙን አስለወጠው እንጂ ምን ሰራለት››
‹‹በአስራ ሰባት መርፌ የጠቀመው ቁምጣ ለውጥ ካላመጣ እኔ የአቋም ለውጥ ላምጣ ብሎ እንደሆንስ?››
‹‹አይመስለኝም፡፡ ነገሩ ሌላ ነው፡፡ በቴዲ አፍሮ የፖለቲካ አቋም ውስጥ ፍቅር ፊቸሪንግ ገባኮ!››
‹‹ምንድን ነው የምታወራው?››
‹‹የቴዲ አፍሮ ጊዜያዊ የፖለቲካ አቋም ለፍተሻ ወደ ተቃዋሚ ላቦራቶሪ መውረድ አለበት፡፡ የሁለት መቶ ሺ ብር
የአልማዝ ቀለበት ለፍቅረኛው ማሰሩን ሰማህ ደ’ሞ?!››
‹‹አይ፤ ከመርካቶ የጎዳና ህፃናት ጋር ፋሲካን አብሮ ቢውል አይሻልም ነበር፤ ነፍሱንም ዝናውንም አንድ ላይ
ለማስኬድ?!››
‹‹ማን ይምከረው፡፡ ምን የዛሬ ዘፋኝ እሱ መካሪ፤ ራሱ ተመካሪ፤ ራሱ አርቲስት፤ ራሱ ሳይንቲስት፤ ራሱ ገጣሚ፤ ራሱ
ዜማ ከግጥም አጋጣሚ፤ ራሱ ኪቦርዲስት፤ ራሱ ጊታሪስት፤ ራሱ ዘፋኝ፤ ራሱ ዘማሪ፡፡ እንደ መድሃኒያለም በአንድ ጊዜ
በሁሉ ቦታ እየተገኘ ቄሳርና እየሱስን አምታታብን’ኮ፡፡…..››
‹‹ይገርማል!››
‹‹እንዳው የምሩ ግን፤ ግለሰብ ግንባታ፣ ማህበረሰብ ግንባታ እና ሙዚቃ እንደ ስላሶች የተዋሃዱ አይመስልህም፤ በዚች
ምስኪን አገራችን? የአገሬ ሰው ሙዚቃን ቅዱስ መንፈስ አድርጎ በትዝታ፣ አንቺዬና አንቺ ሆዬ ሲቆዝም ይውላል፡፡
ከእግዜር ርቆ፤ ከስራ ርቆ፤ በእውኑ ተርቦ፤ በህልሙ ቅቤ ጠጥቶ የውሸት ሲኖር ሳይ እዝናለው፤……›› አለ፡፡
‹‹እንዲህ ትፈላሰፋለህ እንዴ?››
‹‹ትንሽ እውቀት አደገኛ ስለሆነ ይሆናል የሚያፈላስፈኝ፤…..››
‹‹ትንሽ የሚባል ዕውቀት የለም፡፡ ያለችህን ባግባብ ከተጠቀምክ አንተ አዋቂ ነህ፡፡ ለምሳሌ ቴዲ አፍሮ ያለችውን
ዕውቀት በመጠቀሙ የሙዚቃውን ምህዳር በራሱ ሰሌን ጠቀለለው፡፡ ከዚህ ወዲያ ቴዲ አፍሮ በዘንድሮው አልበሙ በመዝፈን
ፋንታ ዘነጠብን ብለህ ብታወራ ምቀኛ ነህ!›› አልኩት፡፡
‹‹ዘንድሮ ቀሽም ዘፈነ እንዴ?››
‹‹የአቤል ሙሉጌታንና ሃይሌ ሩትን ዘፈን ከመስማትህ በፊት ከሰማኸው በርግጥ አሪፍ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮ የሃይሌን
አቤልን ዘፈን ሳይሰማ አልበም ማውጣቱ ሳይጎዳው አልቀረም፡፡ ባገሪቱ የሙዚቃ ባለሙያ ከሌለ እኛው እንተንትነው
እንጂ!…..››
‹‹ወይ ጉድ፤ አንተ ነገረኛ ነህ፡፡ እስኪ እኔም እሰመዋለሁ፤….››
‹‹እስካሁን ሳትሰማው? እውነትም ጨክነሃል!››
‹‹ከቴዲ አፍሮ ዘፈን ይልቅ የቴዲ አፍሮ የ200 ሺህ ብር የጣት ቀለበት ወሬ ነው የመሰጠኝ፤…..፡፡ እስኪ አስበው
ረሃብ ጥርስና ጥፍር አውጥቶ የአዳሜና ሄዋኔን ጨጓራ ሲቧጥጥ በሚውልበት አዲሳባ፤ 200 ሺ ብር አንድ ኢንች
ዲያሜትር ቀለበት ሆኖ፤ ከአንድ አለንጋ ጣት ላይ እንደዋዛ ተሰንቅሮ ያለስራ ሲወዛዎዝ ሲውል ስታይ ፃፍ ፃፍ
አያሰኝህም?›› አለ፡፡
‹‹አንተን ሩጥ ሩጥ አሰኘህ እንዴ?›› ብዬ አሳኩት፡፡
‹‹እውነት እንደ ጋዜጠኛ ይሄ ነገር አያሳስብህም?›› አለ ቀጥሎ፡፡
‹‹በርግጥ ያሳስበኛል፡፡ አንዳንዱ የዚህ ዘመን ፍቅር እንደ ኤሌክትሪክ በማዕድን በኩል ካልሆነ ወደ ልብ አልሄድም
እያለ ችግር ሆነኮ፡፡ ቴዲዬን እሱ ነገር ገጥሞት እንደውሳ፡፡ አትፍረድ፤ ይፈረድብሃል፡፡ ደግሞ ኦሾ ምን ብሏል
መሰለህ፤ ‘ፍቅር እምቢ ካለህ በአልማዝ ቀለበት ምጣበት፤ ልኩን ያገኛል!’››
‹‹ኦሾ እንዲህ አለ እንዴ በናትህ?›› አለ እዬሳቀ፡፡
‹‹ሳይል አይቀርም ብዬ ነው፡፡ መቼስ ኦሾ የማይለው ነገር የለ!››
‹‹እየቀለድክ ነው መሰለኝ፡፡ …….አናዳጁ ነገር ደግሞ ምን መሰለህ?››
‹‹ምንድን ነው?››
‹‹ከጠቅልል ሚኒስትራችን ጋር እኮ ነው ተዛምዶት ያረፈው?!›› አለ ድምፁን ቀነስ አድርጎ፡፡
‹‹እኮ ቴዲ አፍሮ?›› አልኩ ጮክ ብዬ፤ ክፍት አፍ የሆንኩ ልጅ፡፡ እንዳው ምን ይሻለኛል?!
‹‹ታዲያስ!››
‹‹በተሰቀለው! በየት በኩል ባክህ?››
‹‹በናታቸው በኩል ነው አሉ!››
‹‹ሆ ሆ…..ይሄ ነገር እንዴት ነው፡፡ የቀጣዩ አልበም መጠሪያ  ‘ህዳሴው’  የሚል ይሆናል በለኛ!››
‹‹’ብሄር ብሄረሰብ’ ሊባልም ይችላል፡፡ እንደ ሮያል ቤተሰቡ ስምምነት ነው!››
‹‹ወይ ነገር፡፡ እንደ ሰለሞን ተካልኝ ‘ቅንድቡ’ የሚል ነጠላ ለቆ ጉድ እንዳያሰማን እንጂ እባክህ!››
‹‹ያኔማ እስከ ቀይ ባህር ድረስ ነው የማሯሩጠው፡፡….››
‹‹ይሄን ሁሉ መረጃ ግን የት ነው የምታገኘው?›› ስል ጠዬኩ፡፡
‹‹ፌስ ቡክ ነዋ፡፡ ፌስቡክ አያመጣው የለ፡፡ ሰሞኑንማ ተወው፡፡ ፌስቡክህን በከፈትክ ቁጥር ቴዲ አፍሮ ቆሞ፤ እጩ
ባለቤቱ ተቀምጣ፤ በግራ፣ በቀኝ፣ በኋላ፣ በፊት፣ በታች፣ በላይ፤ ወዘተ… ሲሳሳሙ ታያለህ፡፡ ይሄ እውነት ቴዲ
ካሳሁን ነው? ብለህ ልትጠራጠር ሲያምርህ ያቺን ውብ ፈገግታ ብልጭ አድርጎ ‘’አትጠራጠር እኔ ነኝ’’ ይልሃል
ቴዲዬ፡፡ ወይ ጉድ ብለህ ወይም ቀንተህ ወይም በጉምጃት ምራቅህን እንዳትጨርስ ሰግተህ ፌስ ቡክህን ትቆልፍና
ኢሜልህን ስትከፍት የማታውቀው ሰው ሰበር ዜና ብሎ ‘’ቴዲ አፍሮ ቀለበት አሰረ’’ ይሉት ሰባራ ዜና ይልክልሃል፡፡
ምርር ብሎህ ኤሜልህንም ፌስቡክህንም ጠርቅመህ ኖትቡክህን ገልጠህ እውቀት ለመመርመር ቁጭ ባልክበት ስራ ያጣው ቴሌ
የማይመለከትህን ሜሴጅ ይሰድልሃል፤ ብረትን ወርቅ የሚያደርጉ ወርቅ የሆኑ አልኬሚስት ዘመዶቻችን የመሰረቱት ሙዚቃችን
ሊያሳድግ ሊመነድግ የተነሳው አዲሱ የቢዝነስ ሞኖፖሊ የቴዲ አፍሮን ዘፈን ግዛ ይልሃል፡፡ መፅሃፍ ግዛ አይልህም
እኮ፤ መፅሃፍ ከገዛህማ ትበልጠዋለሃ፤ ካርል ማርክስን እየጠቀስክ ሞኖፖሊውን ድባቅ ትመታበታለሃ፤ ስለዚህ በዘፈን
ሊያዘናጋህ ይፈልጋል፤…..›› አለ በምሬት፡፡
‹‹አዲሱ ካፒታሊስት ሙዚቃችን ሊያሳድግ ቢነሳ አታሽሟጠው!›› አልኩት፡፡
‹‹አሁን ገና ልበልጥህ ነው፡፡ ልብህ ሳታድግ፤ ሳንባህ መጠኑ ቢጨምር የካንሰር ተጠቂ ትሆናለህ፡፡ በጣም እርቦህ
ሙዚቃ ሰምተህ ታውቃለህ? ረሃብህ እጥፍ ይጨምራል፡፡ የአገሬ ዘፈን አድጎ የአገሬ ህዝብ በአስተሳሰቡ በቆመበት
የሚረግጥ ከሆነ ማህበራዊ ካንሰር ተከሰተ ይባላል፡፡ ቴዲ አፍሮ ሚስት በማጨቱ አንዳንድ የአገሬ ሴቶች በብስጭት
በረኪና ካልጨለጥን ካሉ ካንሰር ማለት ይሄ ነው፡፡..…›› ሲል መለሰ፡፡
‹‹በጣም የመረረህ ትመስላለህ?›› አልኩት፡፡
‹‹እንኳን እኔ የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ ራሱ ሳይመረው አልቀረም!››
‹‹እንዴት? ደሞ እሱ ምኑ ተነካና?››
‹‹የመሃመድ ቦአዚዝ አብዮት በአረቡ አለም፤ የቴዲ አፍሮና የእጮኛው ፎቶ ሾፕ በአበሻ አለም ፌስቡኩን
ሲያጨናንቁበትሳ!?›› ሲል መለሰ፡፡ እዚህ ላይ ጦሽ ብዬ ነበር የሳኩት፡፡
‹‹ለማንኛውም የአብርሃምና የሳራ ጋብቻ እንዲሆንለት ልመኝ መሰል!›› ሲል ቀጠለ፡፡
‹‹የፀጋዬ እና ፊያሜታን ፍቅር ያድርግለት ማለት አይሻልም?!››
‹‹ፀጋዬና ፊያሜታ እነማ ናቸው ልልህ ነበርኮ፡፡ ኦሮማይን ማንበቤ ትዝ አለኝ፡፡ በነገርህ ላይ የቴዲ አፍሮ ጥምረት
እኔን ጨምሮ የበርካታ ወንዶችን የሞራል ጥያቄ የመለሰ በመሆኑ በአንድ በኩል ይደነቃል!›› አለ፡፡
‹‹እንዴት?››
‹‹እንደምታዬኝ አጭር ነኝ፡፡ ረጂም ሴት አግብቼ ነበር፤ ኋላም ፈታቺኝ፡፡ የሰፈር ሰው ባለፍን ባገደምን ቁጥር
‘ፈረስና ባልደራስ’ እያለ በሽሙጥ ፍቅራችን ደመሰሰው፡፡ ረጂም ሴት ላላገባ ማልኩ፡፡ ረጂም ሴት ለማግባት አጭር
ወንዶች የሚፈሩት ለምን እንደሆነም ገባኝ፡፡ በዚህ በኩል ቴዲ አፍሮ የቁመት ባልደረቦቹን ነፃ ሳያወጣን
አልቀረም!›› አለ፡፡
‹‹ሴቶችኮ ወርቅ ልብ ማዬት ካልቻሉ ወርቅ ማዕድን፤ ወርቅ ማዕድን ማዬት ካልቻሉ ወርቅ ልብ ያያሉ እንጂ ቁመት
አያዩም፡፡ ሚስትህ የፈታችህ በሰፈር ሽሙጥ በቀላሉ የሚታጠፍ ሽቦ ልብህን አይታ እንጂ በቁመትህ ማጠር
አይመስለኝም!›› አልኩት፡፡
ደስ አለው፡፡ ተንደርድሮ መጥቶ ግንባሬን ሳመኝ፡፡
‹‹ከአመታት በፊት በቦክስ ልትተረትረው የነበረውን ግንባር አሁን ስትስመው ምን ተሰማህ›› አልኩት፡፡
‹‹ሃሴት ነዋ! ሃሴት!››
የጠጣሁትን ሻይ፤ የበላሁትን ኬክ ከፈለ፡፡ ‹‹ከሳምንት በኋላ ለውድድር ወደ ኦስሎ ኖሮዌይ እሄዳለሁ፡፡ ስመለስ
እደውልልሃለሁ!›› ብሎ ስልኬን ተቀበለ፡፡
‹‹ስንት ሺ ሜትር ነው የምትሮጠው?›› ስል ጠዬኩት፡፡
‹‹5 ሺ››
‹‹በል የቀነኒሳን ሪከርድ እንዳትሰብር ተጠንቀቅ!›› አልኩት:: (መቼስ የቀነኒሳ ነገር አይሆንልኝ፡፡ ቀነኒሳን
ሰሞኑን አይታችሁታል ወይ? ãረ ኦሎምፒክ ደርሷል ንቃ በሉት፡፡ ያያችሁት ካላችሁ አደራ ንገሩኝ፡፡ ናፍቆኛል፡፡
አቤት ስወደው፡፡ እዩኝ አይል፤ ስሙኝ አይል፤ ሳሙኝ አይል፤ ካልፈረምኩላችሁ አይል፤ ተደብቆ ከርሞ ይመጣና ሪከርድ
ሰብሮ ልማታዊ አርቲስት የሰበረውን ቅስማችን ይጠግንልናል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አንዱ ሲሰብረው አንዱ እየደረሰ
ባይጠግነው ኖሮ ምን ይውጠው ነበር? ወገኔ ግን ሞኝ ነው፤ ከጠጋኙ ትቶ ከሰባሪው ጋር ይውላል፡፡ በሬ ካራጁ
እንደሚውለው፡፡)
‹‹ለምንድን ነው የቀነኒሳን ሪከርድ እንዳልሰብር የፈለከው?›› ብሎ ጠየቀ፡፡
‹‹ቀስ ብሎ ማደግ አይሻልም? ቶሎ ማደግ እኮ ነው አገር የፈታው፡፡ ቀርቀሃ ከወይራ ቀድሞ ያድግና በነፋስ ዝንጥፍ
ብሎ ይወድቃል!›› ብዬ መለስኩለት፡፡
ሳቀ፡፡
‹‹እንደ ቀነኒሳ አሸንፈህ አስፈንጥዘን በናትህ!›› አልኩት ቀጥሎ፡፡
‹‹አትጠራጠር፡፡ ይልቅ ስመለስ አበባ ይዘህ ኤርፖርት እንድትጠብቀኝ!›› አለ፡፡
‹‹ከቴዲ አፍሮ ጋር ማይክ ይዘን እንጠብቅሃለን፡፡ እኔ ለቃለመጠይቅ እሱ ሊዘፍንልህ!›› አልኩት፡፡
እየሳቀ ሄደ፡፡ ቀጥሬው የነበረው ጓደኛዬ ከርቀት ሲመጣ አየሁት፡፡ ከቀጠሮው ሰዓት በጣም ዘግይቶ ነበር፡፡ እንኳንም
ዘገዬ፡፡ እሱ ባይዘገይ ኖሮ ይሄ ወሬ ባልተፃፈ ነበር፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ