ዓርብ 5 ኤፕሪል 2013

ሞተበት ሲላጭ፤ ያልሞተበት ቅቤ ይቀባል (የጉራጌ ተረት)


ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ከአንድ ውጊያ ድል በኋላ፤ እስቲ ያሳለፍነውን ጦርነት እንዴት እንዳሸነፍ
እንመርምር ይባባላሉ፡፡
ነብር - “የእኔ መኖር ነው ዋናው፡፡ የእኔ ፍጥነት ጠላቶቻቸውን አደነጋግሩዋቸዋል” አለ፡፡
ዝሆን - “የእኔ ግዙፍነት ጠላቶቻችንን ብርክ አሲዞዋቸው እንደነበር ሁላችሁም ምስክር ናችሁ” አለ፡፡
ዝንጀሮ - “እኔ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በየዛፉ ላይ እየተንጠላጠልኩ ‘ወዮላችሁ! የአያ አንበሶ ጦር ዶጋመድ
ሊያደርጋችሁ እየመጣ ነው’ ስላቸው ጫካውን እየለቀቁ ሲፈረጥጡ አይታችኋል፡፡ ‘ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው’
የሚባለው ዕውነት መሆኑን ታዝባችኋል፤” አለ፡፡
አጋዘን - “እኔ በስንቅ፣ በትጥቅና በንብረት ጥበቃ ማገልገሌን መቼም አትክዱም፡፡ ዞሮ ዞሮ ዋናው ሁላችንም
የአያ አንበሶ ምልምሎች መሆናችን ነው፡፡ ያ መቼም አሌ አይባልም፡፡ ሁላችንንም የረዳን የሳቸው አቅምና ዝና ነው፡
፡ ድሉም የእሳቸው ውጤት ነው” አለና ተቀመጠ፡፡
ሁሉም በተራ በተራ ዘራፍ እያሉ ራሳቸውን እያደነቁ ተቀመጡ፡፡
በመጨረሻ ጦጢት ተነስታ፤
“እኔ ግን በመጠኑ ቅር ብሎኛል” አለች
“ለምን? ምክንያትሽን አስረጂና?” ተባለች፡፡
ጦጢትም እንዴት ስሜቷን ተቆጣጥራ እንደምትናገር በማስላት፤ ድምፁዋን አጠራችና፤
“ጌቶቼ! ወንድሞቼ! እህቶቼ! ጠላቶቻችንን በወኔ መደምሰሳችን እርግጥ ነው እጅግ አስደሳች ነገር ነው፡፡ ዕድሜ
ለጀግናው መሪያችን፤ በማያወላውል ሁኔታ ድል መትተናቸዋል!! የሚቀጥለውንም ውጊያ እንደምናሸንፍ ምንም
ጥርጥር የለኝም፡፡ ሆኖም ከእኛ ጋር ሊሆኑ የሚችሉትን ሁሉ ከጠላት ጋር ደርበን ማጥፋት ያለወገን ያስቀረናል፤
ብዬ እገምታለሁ፡፡ እና እንደምታውቁት በሌሎች ደኖች ደግሞ እኛን ለማጥቃት ጊዜ የሚጠብቁ በርካቶች እንዳሉ
እናውቃለን፡፡ ዓለም ተገለባባጭ ነው፡፡ አሮጌው ይሄድና አዲሱ ይተካል፡፡ እኛ ሄደን ተተኪው ይመጣል፡፡ ስለዚህ
እንዳለፈው ጊዜ ስለጦርነቱ እንኳ የሚያወራ አንድ አውሬ ሳናስቀር ሁሉንም መደምሰሱ፣ ነገ ይህን ጫካ ለቅቀን
ስንሄድ ወሬ ነጋሪ እንኳ እንዳይቀር ያደርጋል፡፡ ከጠላትም ለዓይነት አንዳንድ ብናስተርፍ ይሻላል፡፡ ደሞም እንደኛ
ሊያስብ የሚችለውን ብንለይና አብረን ብንጓዝ ጥሩ ነው”፡፡
ሁሉም “ጦጢት ውነቷን ነው” አሉ፡፡
***
ሁሉንም ጠራርጌ አጥፍቼ እኔ ብቻ ልቅር ማለት ጐጂ እንደሆነ እናስተውል፡፡ ሁሉን እንደመስሳለን፤ ሁሉን
ድባቅ እንመታለን ያሉ ከሂትለር እስከ ፒኖቼ Apre moi le deluge (እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል) ካለው የፈረንሳዩ
ሉዊ፤ ከቦልሼቪክ ደበኞች፣ በሴራ ተተኪ ነን እስካሉት እስከ “ጋንግ ኦፍ ፎር” በየዘመኑ ገነው ሲጠፉ አይተናል፡፡
ማንም ፊቴ አይቆምም የሚለው የሞንጐሊያዊው ጄንጂስ ካን ታሪክ መልካም ምሳሌ ይሆነናል፡፡
ሞንጐሊያውያን ቻይናን በወረሩ ሰዓት፤ ጄንጂስ ካን የተባለው መሪያቸው አሸንፎ ቻይና ሲገባ፣ ይቺ አገር
ለምንም አትሆንም ብሎ ከማሰብ ተነስቶ “ለፈረሴ እንኳን ለግጦሽ መሬት የሌላት አገር ናት ቻይና፡፡ ድምጥማጧን
ማጥፋት አለብኝ” አለ፡፡ “ለምን ታጠፋታለህ?” ሲባል፤
“እነዚህን ቻይናውያን ከምድረ - ገጽ አጥፍቼ መሬታቸው ላይ ለፈረሴ የግጦሽ ሣር ባበቅል ይሻላል” አለ፡፡ ይሄኔ
አንድ ቹ ሴይ የሚባል ብልህ ሰው፤ እንደምንም ተጣጥሮ የጄንጂስ ካን አማካሪ ሆኖ ነበርና፤ “ቻይናን ከምታጠፋት
እያንዳንዱ ቻይናዊ ቀረጥ እንዲከፍል ብታደርግ ብዙ ገንዘብ ልታገኝ ትችላለህ” አለው፡፡ ጄንጂስ ካን በምክሩ
ተስማማ፡፡ ቀጥሎ ግን አንዲት ካይ ፌንግ የምትባል ከተማ ወርሮ ሊያወድም ፈለገ፡፡ አማካሪው ቹ ሴይ፤ “ጄንጂስ
ካን ሆይ! የቻይና ጠበብት ሁሉ መሀንዲሶቹ፣ ሐኪሞቹ፣ ባለ እጆቹ … ሌሎች ከተሞቻቸው ሲወረሩ የመጡት
ወደዚች ከተማ ነው፡፡ ከተማይቱን ከማጥፋት ለምን በባለሙያዎቹ አትጠቀምባቸውም” ሲል መከረው፡፡ ጄንጂስ
ካን ምክሩን ተቀበለ፡፡ መንገዶች ተሠሩ፡፡ ህንፃዎች ተገነቡ፡፡ ሆስፒታሎች ተቋቋሙ፡፡
“ሰዎችን የሚነዳቸው የግል ፍላጐት ነው፡፡ ይህንን ፍላጐት ለማሳካት የሚያረጉትን ጥረት በማየትና በዘዴ
በማግባባት አገር ልታድን ትችላለህ” ይላል ቹ ሴይ፡፡
ችግሩ የሚመጣው ምክር የማይሰሙ መሪዎች ሲኖሩ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ሰው ቀረጥ እንዲከፍል አድርግ
ሲባል በአንድ ጀንበር ሱሪ ባንገት አውልቅ ልበል ያለ እንደሆን ነው፡፡ የግል ፍላጐታቸው የአገር ካዝና የሚያራቁት
ከሆነ፣ ሙስናው ካጠጠና የዚህ መሸፈኛ ደግሞ “እኔ ብቻ ነኝ” የሚያስችል ሥልጣን ከሆነ አገር አለቀች፡፡
ከዚህ ቀደም ለዚች አገር ህልውና ሲባል መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ዛሬም ነገም ይከፈላል፡፡ መስዋዕትነቱ
የተከፈለው ተወዶ፣ ለውጥ በማምጣት ታምኖ፣ ከልብ ታግሎ ነበር፡፡
የተቀደሰ መስዋዕትነት የሚባለውም ያ ነው፡፡ አግባብ ነው፡፡ አግባብ የማይሆነው ተገዶ፣ ሳያስቡና ሳያልሙ፣
ምናልባትም ለምን እንደሆነ ሳያውቁ መስዋዕትነት መክፈል የሆነ እንደሆነ ነው፡፡ ህዝብ ማናቸውም ነገር ለምን
እንደሚከናወን የማወቅ፣ መረጃ የማግኘት መብት አለው፡፡ ያ ካልተከበረለት በገዛ አገሩ ባይተዋር፣ በገዛ ቤቱ እንግዳ
ይሆናል፡፡ “ሁሉም ነገር ለጽድቅ ነው - ዝም በል” ሲባል አሜን ካለ፤ የአቦ - ሰጡኝ መስዋዕትነት ከፈለ ማለት ነው፡፡
ለልጁ፣ ለትውልዱ የሚያስተላልፈው የመረጃ ቅርስ ሳይኖረው፣ በሕግ አምላክ የሚልበት ልሣን ሳይኖረው፣ አንዲት
የሰለጠነች አገር እየተመኘ ካለፈ፤ ለአገርም ለታሪክም ደግ አይሆንም፡፡
ጠንካራ ተቃዋሚ ስለሌለውም “ይሄ አይሆንም” ብሎ ሽንጡን ገትሮ፣ ታግሎ የሚያታግለው የለምና፣ ውሎ
አድሮ፤ ሁሉንም እየተካሄደ ያለውን ነገር “ይሁን ግዴለም ለበጐ ነው!” የሚልና “ለምን ይሆናል?” ብሎ የማይጠይቅ
ህዝብ ይፈጠራል፡፡ ይሄ አደጋ ነው! አንዱ ከአገር ጋር ሲያለቅስና አገር እንዴት ላድን ሲል፤ ሌለው አገር የሚገድል
ከሆነ፤ ገጣሚው
“..ዘመንና ዘመን እየተባረረ
ይሄው ጅምሩ አልቆ፣ ማለቂያው ጀመረ” እንዳለው ሊሆን ነው፡፡ የመተካካት ዘመን የራሱ አባዜ አለው፤ ሁሉም
እኩል ካልተሳሰበ ግን “የሞተበት ሲላጭ፣ ያልሞተበት ቅቤ ይቀባል” የሚለው የጉራጌ ተረት ዓይነት ይሆናል፡፡
ከዚያ ይሰውረን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ